የ ስደተኞች ምስራቃዊ ጎዞ ዘመናዊ ባርነት

በብዛት ሴቶች የተካተቱበት 500,000 የሚሆኑ ስራ ፈላጊዎች ለ ቤት ውስጥ ሰራተኝነት ወደ ሳኡዲ አረቢያ አንዲጓዙ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተሰምቷል፡ ይህ የአሁኑ እንስቃሴ ወደ ሳኡዲ የሚደረገውን የሠራተኞች ጉዞ ህጋዊ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ጭምር ተገልጿል፡፡ በዚህ የሰራተኞች መላክ ዕቅድ በተለያዩ ሞያዎች ተመራቂ ለሆኑ ስራ ፈላጊዎች ቅድሚያ የሚሰጥ ሲሆን በተጨማሪ በቤት ውስጥ ሰራተኝነት ሲያገልገሉ ሊኖራቸው የሚገባ ክህሎት ስልጠናም እንደ ቅድመ ሁኔታ እንደሚወስዱ ታዉቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከ ሳኡዲ ምንግስት ጋር በፈጠረው የሁለትዮሽ የጋራ ስምምነት መሰረት እየተካሄደ መሆኑን የአደጋ ጊዜ ሪስክ ማኔጅመንት ኮሚሽን በ ሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያብራራ ሲሆን ፣ ኮሚሽኑ ስደት ተመላሾችን በተለይ ከሳኡዲ እና ሊባኖስ ተጠርዘው የሚመለሱትን የተሀድሶ እና መልሶ የማቋቋም ሃላፊነት እንዳለበት የሚታወቅ ነው፡፡             

እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ሰራተኞች ሰርተዉ የሚያገኙትን ገንዘብ ለዚሁ ተብሎ በሚከፈት የባንክ አካውንት እንዲያስቀመጡ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህም በጥቁር ገበያ የሚደረገውን የገንዘብ ምንዛሬ ለማስቀረት የታለመ ነው ተብሏል፡፡ ይህ በስምምንት የሚከናወን ጉዳይ ኢትዮጵያ የገባችበትን የውጭ ምንዛሬ እና ኢኮኖሚያ ጫና ለማቃለል በምፍትሄነት የተወሰደ እና የጋራ ስምምንት የታከለበት መሆኑ ጭምር ተዘግቧል፡፡         

ትልቁ እና አሁንም ያልተመለሰው ጥያቄ ግን እስካሁን ማስቆም ያለተቻለው እና የቀጠለዉ ፆታዊ እና አካላዊ ጥቃቶች ባሉበት ሁኔታ ለሰራተኞቹ ሊደረግ የሚገባው የሰብአዊ እና የአሰሪና ሠራተኞች ስምምነት መብት ጥበቃ መግባባት ስምምነት ባልተደረሰብት አግባብ አሁንም በስፋት ወዳልተለወጠ ተመሳሳይ የስራ ሁኔታ ሠራተኞችን የመላክ ጉዳይ ነው፡፡ 

በስደተኞች ጉዳይ ላይ መልስ በመስጠት ተሳታፊ የሆኑ በርካት አለም አቀፍ፣ ሀገር በቀል እና የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ተቋማት ለስደተኞቹ ድምፅ በመሆን ፣ መረጃዎችን በማጋራት ፣ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የማይግሬሽን ሪስፖንስ ፕላን  በ አፍሪካ ቀንድ እና የመን ያለዉን የስደተኞች ሁኔታ በሚተነትነው ርፖርቱ ወደ 84 ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት በጀት ፈንድ እንዳደረገ እና ከዚህም ፈንድ ትልቁ ተጠቃሚ የሆኑት ሶስቱ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ ፣ የመን እና ሶማሊያ መሆናቸውን ሲሆን እያንዳንዳቸው 32.6 ሚ፣ 23.7 ሚ እና 16.1 ሚ ዶላር በቅደም ተከተል ተበጅቶላቸዋል፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ በኢትዮጵያ ያለውን የበጀት ስርጭት ስናይ በተለይ አምስት የሚሆኑት ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማለትም አይ ኦ ኤም 19.5ሚ፣ ቢታኒ ክርስቲያን ሰርቪስስ ግሎባል 2.1ሚ፣ ብራይት ስታር ሪሊፍ ኤንድ ደቨሎፕምነት አሶሴሽን 2.07 ሚ፣ ሴቭ ዘ ቺልድረን ኢንተርናሽናል 1.5 ሚ እና አጋር ኢትዮጵያ ግብረሰናይ ድርጅት 970 ሺ የአሜሪካ ዶላር ተመድቦላቸዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት ለስደተኞች እና ስደት ተመላሾች የመልሶ ማቋቋም አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ማህበራዊ የድጋፍ አገልግሎቶችን ለመስጠት ኃላፊነት የተጣለባቸው ናቸው፡፡

ምንም እንኳን በሁለቱ መንግስታት መካከል የተደረሰው ስምምነት ህጋዊነትን ቢያበረታታም አሁንም በህገወጥ መንገድ የሚደረገው የሰራተኞችን /ስደተኞችን ጉዞ ማስቆም የቻለ አይመስልም፡፡ ቢንስ ከዚህ ቀደም የታዩት እውነታዎች የሚነግሩን ሀቅ ይህንኑ ነው፡፡ 

ስደተኞችን ይህንን ህገወጥ እና ለህይወት አደገኛ የሆነ የስደት ጉዞ እንዲመርጡ የሚያደርጓቸው በርካታ ገፊ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፤ ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ ድቀት፣ አለመረጋጋቶች፣ የእርስ በእርስ እና ብሄር ተኮር ግጭቶች፣ የስነ-ምህዳር መዛባት፣ ድርቅ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚህ አደገኛ ህገወጥ ጉዞ ሂደት ለህይወት አደገኛ የሆኑ ለሞት የሚያበቁ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የዉሃ ጥም፣ አደገኛ የሆነ የሃሩር ንዳድ፣ ረሀብ፣ አደገኛ የሆነ የመጓጓዣ መንገድ የመሳሱለት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

የመን ከኢትዮጵያ ለሚነሱት ህገወጥ ስደተኞች ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለሚደረገው ጉዞ ዋነኛ መግቢያ መንገድ ናት፡፡ የመን ያለው የሁቲዎች እና በሳኡዲ የሚደገፉት የመንግስት ታጣቂዎች ግጭት ለስደተኞች ከፍተኛ የሆነ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ስደተኞች በዚህ ጉዞ ውስጥ ለማለፍ ያላቸውን ጥሪት ሁሉ ለመሸጥ ይገደዳሉ፡፡ የሚያገኙትንም ገንዘብ ለጉዞ አመቻቾች ክፍያ ፣ ለትርንስፖርት እና ሌሎች ህጋዊ ሰነዶችን ለማዘጋጀት ያዉሉታል፡፡ አሁን እየታየ ካለው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት ከመከሰቱ በፊት ቀደም ባሉ ጊዜያት አንድ ስደተኛ ለ ደላሎች እሰከ 18ሺ የኢትዮጵያ ብር ድረስ መክፈል ይገደዳል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ደላሎች በእነዚህ ስደተኞች ህይወት ላይ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሲሆን  ስደተኞች ሊገጥማቸው የሚችለውን አደጋ ግልፅ ባለማድረግ ፣ የማሳመን የመመልመል እና የመላክ ስራ ይሰራሉ፡፡ ሴቶች በቤት ውስጥ ሰራተኝነት፣ ወንዶች ደግሞ የግብርና ስራዎችን እንዲሰሩ ይገደዳሉ፡፡ ባልጠራ እና የጋራ ስምምነት ባልተደረሰብት የአሰሪና ሰራተኛ ህግ የስደተኞች ሰብኣዊ መብት ከለላ ባላገኘበት ሁኔታ ስደተኞችን ደላሎቻቸው ሳኢዲ እንዲያደርሷቸው ከፍተኛ ከፍያ የሚከፍሉ ሲሆን ባብዛኛው ስደተኞቹ የሰሩበትን ክፍያ አይገኙም፣ ይህም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙት ወደ ዘማናዊ ባርነት ያደላ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡   

error: