Celebrating Shadey, Ashendeyay, and Solel

Women celebrating the annual festival known by it’s various names: Shadey, Ashendiyay, and Solel

የሻደይ ታሪክ በዋግና በላስታ፣ በትግራይ፣ በራ ያና ቆቦ አካባቢ የበዓሉ ታሪካዊ አጀማመር በማስመልከት በቀሳውስት ዘንድ በስፋት የሚነገር ነው፡፡ ታሪኩም ከቅድስት ድንግል ማሪያም ገድላት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይወሳል፡፡ የሻደይ በዓል የሚከበረው የፍልሰታ ፆም መፍታትን ምክኒያት በማድረግ ሲሆን << ፍልሰታ>> የሚለው ቃል ደግሞ ዶክተር አጸደ ተፈራ በ2ዐዐዐ ዓ/ም የሻደይ መጽሄት ላይ የቤተክርስቲያን አባቶችን ጠቅሳ እንዳሰፈረችው፣ <<የእማቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ስጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን ኋላም በገነት በእፀ ህይወት ስር ከነበረበት መነሳቱን>> የሚያመላክት ቃል ነው፡፡ <<ፍልሰታ>> የሚለው የግእዝ ቃልም በአማርኛ ቋንቋ ቀጥታ <<መፍለሷ>> የሚለውን ቃል የሚወክል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡


የቤተክርስቲያን አባቶች የሻደይ በአልን አጀማመር ከእመቤታችን ጋር አያይዘው ከመጥቀሳቸው ባሻገር፣ በአሉ በአመዛኙ በልጃገረዶች  ብቻ የሚዘወተር መሆኑ በራሱ ከእመቤታችን ጋር ተዛማጅነት እንዳለው የሚያስጠረጥር ሌላ ማሳያ ነው፡፡ የቀድሞው የዋግ-ኽምራ ሃገረስብከት  የስብከት ወንጌል መምሪያ ሃላፊ የነበሩት መጋቤ ምስጢር ገብረሂወት ኪዳነ ማርያም ይህንን አስመልክተው የተናገሩት <<በዓሉ በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው በሄዋን ምክኒያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመክፈቱ ነው>> ካሉ በኋላ በዚህም መመኪያቸው ስለሆነች ልጃገረዶች በአሉን ያከብሩታል፡፡ ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት በእርሷ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡


እኝህ አባት በሌላ አቅጣጫ የሻደይ በአልን የኖህ ዘመን ልምላሜ ተምሳሌት አድርገው የሚወስዱ አባቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ እመቤታችንም በኖህ መርከብ እንደ ምትመስል አስረድተዋል፡፡ ተምሳሌቱንም ሲያብራሩ <<የሰው ልጅ በኖህ መርከብ ከጥፋት እንደዳነ ሁሉ በልጇ ያመኑና በእርሷ የአምላክ እናትነት የተማጸነ ሁሉ ይድናሉ፡፡ በዚህም በኖህ መርከብ ትመሰላለች>> ብለዋል፡፡ አክለውም <<የሻደይ ቅጠል የኖህ ርግብ ያመጣችው የለመለመ ቅጠል ተምሳሌት  እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ልጃገረዶች ቅጠሉን እያስከረከሩ መጫወታቸው  ወይም መሽከርከሩ ደግሞ እያሸበሸቡ እመቤታችን ያሳረጓትን መልአክትን ይዘክራል>> ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ሁለት አተራሪኮች የሻደይ በአል አከባበር ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋርም ይሁን ከኖህ መርከብ ጋር ተዛማጅነት እንዳለው መመልከት ይቻላል፡፡
እስካሁን ባለን መረጃ መሰረት የሻደይ በአል የሚከበረው ከክርስትና እምነት መጀመር በኋላ በቅድስት ድንግል ማርያም እርገት አማካኝነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የክርስትና እምነት የተቀበለችው እ.አ.አ በ331 መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአገው ህዝብም በውድም በግድም ከኦሪት እምነቱ የተናጠበው  በስድስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ አንፃር የሻደይ በአል ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ተከብሯል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ታሪካዊ ባህል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚገኙ ተፈጥሮአዊ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ውስጥ አንዱ እና  በወርሐ ፆመ ፍልሰታ ሁል ጊዜ በየአመቱ በ16ኛው ቀን በድምቀት የሚከበረው የሻደይ በዓል ጨዋታ ነው፡፡


ሃዋሪያት ቅድሳን አንዕስት፣ ደናግል፣ ፃድቃንም የቅድስት ድንግል ማሪያም የእርገት በዓሏን በየአድባራቱ ነሃሴ 16 ቀን በየአመቱ በዝማሬና በእልልታ በተመሳሳይ ያከብሩት እንደነበር በሰፊው ይነገራል፡፡
ይህም በተዋረድ ትስስርና ትልቅ ታሪክ ባለው ሃይማኖታዊን በዓል ምዕመኑ ተቀብሎ በነጫጭ  አልባሳትና ጌጣጌጥ እንዲሁም ለማሸብሸብ እንዲያመች ሴቶች የሻደይ ቅጠል  ወገብ ላይ በማሰር እንሆ ሻደይ በድምቀት እየተከበረ  ይገኛል፡፡


ስለ ሻደይ በዓል ጨዋታ አመጣጥ ሃይማግታዊ ይዘትና  ትስስር  ያለው መሆኑን ከተገነዘብንና በይበልጥ የሴቶች ባህላዊ ጨዋታ መሆኑን ካወቅን ሻደይን በሃገር ውስጥ በተመረቱ አልባሳትና ጌጣጌጦችን በመልበስ ማክበር እንደ ግለሰብ አዋቂነት እንደ ቡደን ክብር እና ኩራተ ነው፡፡ ባህላችን የማንነታችን መገለጫ ነው የምንለው ሌላ በውጭ ሃገር የተፈበረኩ ባዕድ ነገሮችን ሳናቀላቅል በሃገር ውስጥ የተመረቱ አልባሳትንና ጌጣጌጦችን ስንለብስ ነው፡፡
በእዚህ ዙሪያ ለሻደይ በዓል ጨዋታ አስፈላጊ ባህላዊ አልባሳትን ከሞላ ጐደል እንሆ
• አልባሳት፡- ቀሚስ፣ መቀነት ፣ ጫማ፣ ሻሽ —
• የፀጉር ስሬት፡- ግልብጭ፣አንድ እግራ፣ ግጫ ፣አልባሶ፣ሳዱላ፣ ጋሜና ቁንጮ፣ ጐፈሬና፣ የእንጨት ማበጠሪያ
• ጌጣጌጦች፡- ኩል፣ ድሪ፣ ድኮት፣ አልቦ፣ ዛጐል፣ ጠልሰም መስቀል፣ አምባር፣ ማርዳ፣ ድባ፣አሸክት፣ስቃጫ  የመሳሰሉትን በመልበስ እናቶች፣ ልጃረገዶችና ህፃናት የሻደይ በአል ጨዋታን በድምቀት ያከብሩታል፡፡
የተዘጋጁ ያማሩና የተዋቡ ሴቶች አልፎ አልፎ በዙሪያቸውን በታጀቡ ጐርሞሳዎች ይጠበቃሉ፡፡
ሻደይ በጣም ያሸበረቀና የሚስብ የሴቶች በዓል ነው፡፡ የሻደይ ቃል የተወሰደው ከቅጠል ነው ይህንም ቅጠል ለዝግጅቱ በዓል ይጠቀሙታል በዓሉም በየአመቱ ነሃሴ 16-21 ይከበራል፡፡ በዓሉ ሃይማኖታዊም ታሪክ አለው በመሪያቸው አማካይነት ከሃይማኖታዊ ቦታ ከቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ይሰበሰባሉ በትንሳኤውም ይወጣሉ በአራቱም አቅጣጫ ያሉ ቡድኖች ይገናኛሉ የምስጋና ዘፈኖችን ከቤተክርስቲያን ካደረሱ ቡኋላ ወደ ሌሎች አለማዊ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ የሴቶች በዓል የሆነ ታሪክ ነው በዓሉም የሚዘጋጀው በባህላዊ ቀለማት ባሸበረቁ ልብሶችን ለብሰው ይውላሉ፡፡ በዓሉ የባህላዊ አልባሳትን አይነቶችና የሴቶችን ባህላዊ ዘፈን ውድድር ለማየት ምቱ አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ጫወታቸውን ሲጀምሩ በአቅራቢያቸው ባለ ቤተክርስቲያን በሰላምና በጤና ለዝግጅቱ ስለመድረሳቸው ከሻደይ ቅጠል ቆርጠው ወደ ቤተክርስቲያኑ ስጦታ ይጥላሉ ቀጥሎም ለቀጣይ አመት በሰላምና በጤና እንዲያደርሳቸውይፀልያሉ ምስጋናም ያቀርባሉ ከዚያም ወደ ተከበረ ትልቅ ሰው ወይም መሪ በመሄድ ባህላዊ ዘፈኖችን ያቀርባሉ እናም ስጦታም ይቀበላሉ፡፡ከዚያም ወደ እያንዳንዱ ሰው የመኖሪያ ቤት በመትመም እያዜሙ “አስገባኝ በረኛ አስገባኝ ከልካይ እመቤቴን ላይ” በማለት በሻደይ ጨዋታ ዙሪያ ከ16 በላይ ጣዕመ ዜማዎችን እያፈራረቁ ይዘፍናሉ፣ ይሸለማሉ፣ ይመረቃሉ፡፡

በመሆኑም ባህላዊ አሴቶችንም ከልማት ጋር በማስተሳሰር የቱሪስት መስህብ ይሆኑ ዘንድ የገቢ ምንጭ መፍጠር እየቻልን በመረጃ እጦት ተዳፍነውና ተሰውረው የሚገኙ ትኩረት ያልተሰጣቸውና ያልተዳሰሱ በርካታ ሃብቶች እንዳሉንም ጥርጥር የለውም፡፡
ሻደይ ከጥንት ጀምሮ ተያይዞ መምጣቱን መረጃውን በሰጡን የሃይማኖት አባቶችና እናቶች መሰረት አስካሁን ድረስ ባህላችን በድምቀት እያከብርን መጥተናል ሌሎች ደማቅና ማራኪ ባህላዊ ጨዋታዎችንና እንዲሁም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብቶቻችንም ጭምር በመረጃ ተደግፈው ሊያዙ ይገባል፡፡ መረጃ የተዘጋንና የተደበቀን ግዙፍ ነገር መክፈቻ የሰረገላ ቁልፍ መሆኑን በመገንዘብ ሃበቶቻችን ሊባክኑ ወይም ደብዛቸው ሊጠፋ አይገባም፡፡  ወንዝ አይፈሬው የሻደይ ቅጠልም ከብዝሐ ሕይወት አንዱ በመሆኑ ዕፅዋቱ ሊስፋፋና ሕልውናው ሊከበር ይገባል እንላለን፡፡

error: