የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአጼ ምኒልክ በተመራው የኢትዮጵያ ሠራዊትና ባህር አቋርጦ ከአውሮፓ ከመጣው የጣሊያን ሠራዊት ጋር የተካሄደው የዓድዋው ጦርነት በታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱ ጉልህ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ አርበኞች የዓድዋ ድል ጣሊያን አፍረካ ውስጥ በተለይ ደግሞ በምሥራቁ የአህጉሪቱ አካባቢ ለማስፋፋት አቅዳ የተነሳችለትን የቅኝ ግዛት ዕቅድን ያጨናገፈ ከመሆኑ ባሻገር፤ በዘመኑ የአውሮፓዊያን ሠራዊት በአፍሪካዊያን ካበድ ሽንፈት ሲገጥመው የመጀመሪያ በመሆኑ ድንጋጤንም ፈጥሮ ነበር።

በወቅቱ

ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ ‘ ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ፤

ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻለብቻ፤

***

የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፤ ተብሎ ተገጥሞም ነበር፡፡

የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የመላው ዓለም ተፈጥሮአዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሠው፤በእውነትና በፍትህ ህልውናና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው … በአድዋ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ስንሄድ 1066 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ታላቁ ጦርነት የተደረገበትና ታላቁ ድል የተገኘበት ሥፍራ አድዋ ከተማና የከተማው ግድም ገመገሞች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያውያን አቡሻኽር (Julian calendar) የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም፤ ወይም በአውሮጳውያን የዘመን አቆጣጠር (Gregorian Calendar) February (የካቲት) መጨረሻ እና March (መጋቢት) መጀመሪያ ላይ 1896. ለጦርነቱ መነሻ የሆነው ውል የተፈፀመው በዚሁ ዘመን ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 468 ኪሎ ሜትር ርቀት ግድም ከውጫሌ ከተማ ግርጌ ከአምባሰል ተራራ ሥር ወሎ ውስጥ ንጉሥ ይስማ እየተባለ በሚጠራ ሥፍራ ነው፡፡በዚህ ውል አንቀጽ 17 ላይ በጣሊያንኛ የሰፈረው ጽሑፍ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በጣሊያ በኩል መሆን እንዳለበት ሲያመለክት የአማርኛው ግን ግንኙነቱን በኢጣሊያ በኩል ማድረግ ትችላለች ይላል።

ይህ የትርጉም ልዩነት እንደታወቀ መጀመሪያ ላይ አጼ ምኒልክ የውሉን አንቀጽ አስራ ሰባት እንደማይቀበሉ ካሳወቁ በኋላ ቀጥሎም የውጫሌውን ውል ሙሉውን ውድቅ አደረጉት። ይህም ጣሊያን ጦሯን በማዝመት ወረራ እንድትፈጽም ሊያደርጋት እንደሚችል የተረዱት ንጉሡ ዝግጅት ማድረግ ጀምረው ነበር።

የተፈራው አልቀረም የጣሊያን ሠራዊት ለወረራ እንቅስቃሴ ጀመረ። ከኢትዮጵያ በኩል የንጉሡን ጥሪ ተከትሎ ከመላዋ አገሪቱ የተሰባሰበው ሠራዊት አገሩን ከጣሊየን ወረራ ለመከላከል ያለውን መሳሪያ ይዞ ወደ ሰሜን አቀና።

በአጼ ምኒልክ የተመራው ሠራዊት እስከ ሃያ ሺህ የሚደርሱ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከአንድ መቶ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አርበኛ ወደ አድዋ ሲተም መነሻው ከአዲስ አበባ ነበር። ሠራዊቱ ዓድዋ ለመድረስ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር አካባቢ በእግሩና በጋማ ከብት መጓዝ ነበረበት።

ሸልዶ ተራራ ወይም (ሶሎዳ ተራራ)፤ ማርያም ሸዊቶ፤ አዲ ተቡን፤ ረቢ አርእየኒ (እግዚሃር አሳየኝ)… በመሠኘት የሚታወቁት እነዚህ ገመገሞችና ተራራማ ሥፍራዎች ዋነኞቹ የጦር ግንባሮች ናቸው፡፡ በመቶ ሺህ የሚሠላ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የአውሮጳ ቅኝ ገዢ ወራሪዎችን ድባቅ ከመታና ረግጦ ካስወጣ በኋላ ከምሽቱ አራት ሰዓት ግድም (የካቲት 23 ቀን) እንዳማርያም ላይ ተሰባስቦ በአንድ እግሩ ቆሞ ቀኙን (ድሉን) ለሰጠው አምላክ ምሥጋና አቅርቧል፡፡ አባት ሆይ፤ ንቀውን የመጡ የአገራችንን ድንበርና ልዕልና የደፈሩ የአውሮጳ ኮሎኒያሊስት ወራሪዎችን እንድናሸንፍ (ድል እንድናደርግ) ስለረዳኸን እናመሰግንሃለን …

ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮጳ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ይለናል የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፉ ላይ፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሰ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ ባበደ መንፈስ (በተቆጣና በቆረጠ መንፈሥ) በጀግንነት ተዋግቷል፡፡

ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል፤በሺዎች የሚቆጠሩ የጣሊያን ሠራዊት አባላት ሲገደሉ ሌሎች ሺህዎች ደግሞ ተማርከዋል።የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የኢጣሊያ ወታደሮች ጋር ሸሽቷል፡፡

በዚህ ድብልቅልቅ ያለ ውጊያ ከሃምሣ ስድስቱ የኢጣሊያ መድፎች በተጨማሪ ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች በአሥር ሺሆችና በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር ተማርከዋል፡፡ በአጠቃላይ ምርኮው ወደ አዲስ አበባ የተጓጓዘው በአምስት መቶ አጋሰሶች ተጭኖ ነው፡፡

በማግስቱ የካቲት 24 ቀን 1888 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ የኢጣሊያ ምርኮኞች በምኒሊክ ድንኳን ፊት ሲያልፉ የኢትዮጵያ ጀግና የገበሬ ሠራዊት እየፎከረ እየሸለለ አሳልፉዋቸዋል፡፡ ጄኔራል አልቤርቶኒ በምርኮኛነት ኢትዮጵያ ውስጥ ቆይቶ አገሩ ከተመለሰ በኋላ በፃፈው መጽሐፍ ላይ ከሚፎክሩት ጥቁር የነፃነት ተዋጊዎች መሃከል አንዱ እንደ እኛው ነጭ አውሮጳዊ ነው ብሎአል፡፡ ይህ ሰው ከፈረንሣይ አገር ወደ ኢትዮጵያ ለጦር መሣሪያ ጥገና የመጣ ካፒቴን ኦርዲናንስ ሲሆን፤ አሁን ጊዜው የጦርነት ስለሆነ ወደ አገርህ ተመለስ ቢባል ቢሠራ አሻፈረኝ ብሎ ከእኛ ጋር አድዋ ድረስ የዘመተ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ላይ ከተዋጋችባቸው የጦር መሣሪያዎች ሠማንያ ሺህ የሚሆኑት አሮጌ ጠመንጃዎች የተገዙት ከፈረንሳይ አገር በምሥጢር ነው፡፡ ጠመንጃዎቹን ገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት በሥጋ በደምና በትውልድ አርመናዊ በነፍስና በመንፈስ በዜግነትና በልብ ፍቅር ኢትዮጵያዊ የሆኑት የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ ሰርኪስ ቴሪዝያን ናቸው፡፡

የጦርነቱ ውጤት

የዓድዋ ጦርነት ድል ለጣሊያኖች ሽንፈት አስከትሎ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከማጽናት ባሻገር ከአድማስ ተሻግሮ አህጉራትን አቋርጦ የተሰማ ጉልህ ተጽዕኖን በዓለም ዙሪያ አስከትሏል።

በዘመናዊው ዓለም የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ተደጋግሞ ከሚነሳባቸው ክስተቶች መካከል አንዱ ለመሆን ከመብቃቱ ባሻገር በተለይ ደግሞ በጥቁሮች ዘንድ የዓድዋ ድል ለነጻነት በሚያደርጉት ትግል ውስጥ መነቃቃትንና ተስፋን የሰጠ ክስተት ሆኗል።ታላቁ የጥቁር ህዝቦች ድል (የአድዋ ድል) በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች አምጥቶአል፡፡ የእንግሊዝ ጋዜጦች በአድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪቃ ተቀሰቀሰ …ብለው ፃፉ፡፡ በኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፡- ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠረ የተባሉት ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በሌሉበት (እርሳቸው በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ) የአፍሪቃና የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተመረጡ፡፡

ጦርነቱ ከመደረጉ በፊት እ.ኤ.አ በ1880ዎቹ መጀመሪያ ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ላይ በተደረገው የአውሮጳ ቅኝ ገዢ (ኮሎኒያሊስት) መንግስታት ሥልጣናትና ልሂቃን የጦር ጄኔራሎችና ሊቃውንት ስብሰባ ላይ ጥቁር ትልቅ ትል ነው ቅንቡርስ ነው እንጂ ነፍስ ያለው ሰው አይደለም ብለው የነበሩ አፈሩ፤ እውነትና ፍትህ ኢትዮጵያና አፍሪቃ ከበሩ፡፡ 

ከፈረንጅ የአውሮጳ መንግሥታት ሩሲያና ፈረንሳይ የአድዋን ድል ከልብ ደገፉ፡፡ ጀኔራል ባራቴሪ በአገሩ በኢጣሊያ ጦር ፍርድ ቤት ቀርቦ ማዕረጉ ተገፈፈ፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲኞር ክሪስፒ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ፡፡

የኢጣሊያዊው ንጉሥ አማኑኤል ኡምቤርቶ የልደት ቀን የሀዘን ቀን እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ሮማ (ሮም)ን ፍሎሬንስን ሚላኖ (ሚላን)ን ቬነስን…የመሳሰሉ የኢጣሊያ ከተሞች ምኒሊክ ለዘላለም ይኑር በሚሉ የተቆጡ አውሮጳውያን ትዕይንተ ህዝብ አድራጊዎች ተጥለቀለቁ፡፡ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ወቅት በዋናው የጦር ግንባር ገጥማ በፍልሚያ ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአራት መስክ ሠለጠነች በምትባለው አውሮጳዊት አገር ኢጣሊያ ላይ ድል ተቀዳጅታለች፡፡ ይኸውም፡- በጦርነት እና በወታደራዊ መረጃ (Military Security intelligence)፤ በዲፕሎማሲና በፖለቲካ ጥበብ ነው፡፡

በወታደራዊ መረጃ (Military Security intelligence) ብልጫ የኢንቲጮ ተወላጅ በሆኑት ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት አማካይነት ኢትዮጵያ ሠለጠነ የተባለውን የአውሮጳ ኃይል አሸንፋ ጣሊያኖች ባልፈለጉት ቦታና ባልመረጡት ጊዜ ወደ ጦርነት እንዲገቡ አድርጋለች፡፡በወታደራዊ ሣይንስ (Military Science) አገባብ ለጦርነት የተንቀሳቀሰ አንድ ሠራዊት ወዲያውኑ ወደ ጦር ግንባር መግባት አለበት፡- ይሄ አንድ ነጥብ ነው፡፡ ሌላው ነጥብ አንድ ለግዳጅ የተንቀሣቀሠ ሠራዊት ለመሰናዶም ሆነ ለመከላከል ውጊያ በአንድ የመከላከያ ወረዳ ከሠፈረ በዚያ መከላከያ ወረዳ ከስድስት ወራት በላይ መቆየት የለበትም፡፡ በአንድ ቦታ ላይ ከስድስት ወራት በላይ ከቆየ ሊደርስ የሚችል የወታደራዊ ሥነልቦና (Military Psychology) ጉዳት አለ፡፡ የመሸገበትን የመከላከያ ወረዳ እየተለመማመደ ሲሄድ ስለሚዘናጋና የውጊያ ስሜቱ እየቀነሰ (እየቀዘቀዘ) ስለሚመጣ ጉዳት አለው፡፡ ከሎጂስቲክ አኳያ የውጊያ ዝግጁነቱም አደጋ ላይ ስለሚወድቅ (በሌላ አነጋገር ስንቅ እየጨረሰ ስለሚሄድ) በነዚህ ምክንያቶች በአፋጣኝ ወደ ጦርነት መግባት ለሠራዊቱ ድል አድራጊነት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡

የኢትዮጵያ በሠላም ጊዜ ገበሬ በጦርነት ጊዜ ጀግና ተዋጊ እንጂ ዘመናዊ ወታደራዊ መሠረት ያለው  Professional Army ባልነበራት በዚያ ዘመን ለአንድ መቶ ሃያ ሺህ ሠራዊት የሎጂስቲክ አገልግሎት እየሰጡ ለረጅም ጊዜ መቆየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የጀግንነት ግለት ሳይበርድ የሎጂስቲክ (ስንቅ ትጥቅ መድሃኒት) አቅም ሳይዳከም በፍጥነት ጦር መግጠም እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጦርነቱን ፈጥኖ ለመግጠም ጣሊያኖች ወደ አድዋ መምጣት አለባቸው፤ ወይም ደግሞ የእኛ ሠራዊት ጣሊያኖች ወደመሸጉበት የኤርትራ ከፍተኛ ቦታዎች መሄድ አለበት፡፡ ከነዚህ ሁለት ሁኔታዎች የአንደኛው መሆን የግድ ነበር፡፡ ወደ ጣሊያኖች መሄድ ከፖለቲካ ሁኔታዎች ባሻገር ከወታደራዊ ሳይንስ አንፃር የሚመረጥ አይደለም፡፡ በምሽግ ውስጥ ሆኖ የሚከላከል ሠራዊትና ከምሽግ ወጥቶ የሚያጠቃ ሠራዊት መስዋዕትነት የመክፈል ዕድሉ እኩል አይደለም፤ ለሚከላከል አንድ ወታደር ሶስት የሚያጠቃ ወታደር ነው የሚያስፈልገው፡፡

ስለዚህ ጣሊያኖች ወደ አድዋ እንዲመጡ ማድረግ የግድ ሆነና የአድዋ ድል ቁልፍ የምላቸው የአርባ ዓመቱ ጐልማሣ ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት ተጠሩና ለአንድ ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት እንዲሠናዱ ተደረገ፡፡ ይሄ ሁሉ በምሥጢር ነው የተከወነው፡፡ በሚቀጥሉት ቀናት አውአሎም ለኢጣሊያ ኮሎኒያሊስት ወራሪዎች ከሚሠልሉ የአገር ተወላጆች (ፌርማቶሪዎች) ጋር ወደ ባራቴሪ ተላኩ፡፡ ከመሄዳቸው በፊት ስንቅ ማለቁና ተስቦ በሽታ በሠራዊቱ ውስጥ መግባቱ ፌርማቶሪዎች ባሉበት ተለፈፈ፡፡ አውአሎምና ፌርማቶሪዎቹ ወደ ኤርትራ ዘልቀው ለጄነራል ባራቴሪ ይሄንኑ ነገሩት፡፡

ባራቴሪ ጊዜው አሁን ነው አለና የካቲት 22 አመሻሽ ላይ በአውአሎም መሪነት ሠራዊቱን ይዞ ወደ አድዋ ተመመ፡፡ የካቲት 21 እንዳይነሣ ዝናብ ስለያዘው እንጂ ታላቁ ጦርነት የካቲት 22 ሊደረግ ይችል ነበር፡፡ ስለዚህ ጄነራል ባራቴሪ በዝናብ በመያዙ ምክንያት ዘመቻውን በማግሥቱ አደረገና የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዝ አድሮ ሊነጋ ሲል የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም አድዋ ጦር ግንባር ደረሠ፡፡ አውአሎም ከፊት ለፊታቸው የጀግናው የቱርክ ፓሻ የአፍሪቃ ጀኔራል አሉላ አባነጋ የገበሬ ሠራዊት ምሽግ እንደታያቸው መሮጥ ጀመሩ፡፡ ባራቴሪ፡- አውአሎም አውአሎም ብሎ ተጣራ፡፡ እስሀ ዝዋአልካዮ አያውለና ብለውት ዘለው አሉላ ምሽግ ውስጥ ገቡ፡፡ ዛሬ አንተን አያድርገኝ ማለታቸው ነው በአማርኛ፡- እስሀ ዝዋአልካዮ አያውለና፡፡

ከጥቂት ደቂቆች በኋላ ምድር ቁና የሆነችበት ድብልቅልቅ ያለው ጦርነት ተጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ጀግና የገበሬ ሠራዊት ከጠዋቱ አራት ሠዓት ግድም ታላቁን የአድዋ ድል መቀዳጀቱን አረጋገጠ ፡፡ ብዙ ሺህ የኢጣሊያ ወታደሮች በጦር ሜዳ ተገደሉ፡፡ ብዙ ሺዎች ደግሞ ቁስለኛና ምርኮ ሆኑ፡፡ የተቀረውንና ድል ተመትቶ የተበታተነውን የኢጣሊያ ወታደር እያሣደደና እያባረረ አፍሪቃዊው ኃይል ፈጀው ብሎ ፅፎአል ጆርጅ በርክሌይ፡፡ ከሚሸሹት መሃከል አንዱ የአውሮጳዊው ወራሪ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ነው፡፡

ይሄ (በአውአሎም ብስለትና ሥልጡንነት መስዋዕትነትና ኢትዮጵያዊ ፍቅር የተገኘው) ሰለጠነ በሚባለው የአውሮጳ ኃይል ላይ አልሰለጠነም በሚባለው አፍሪቃዊ ኃይል የተጨበጠ ትልቅ የወታደራዊ መረጃ (Military Security intelligence) ብልጫ ወይም ድል ነው፡፡

በወታደራዊ ሣይንስ ደግሞ ወታደራዊ መረጃ ለወታደራዊ ግጃጅ አፈፃፀም ዋነኛና ወሣኝ ጠቀሜታ አለው፡፡ በዚህች ዓለም ላይ ከተደረጉ አብዛኞቹ ጦርነቶች ድል ያደረጉት የወታደራዊ መረጃ ብልጫ የነበራቸውና ፍትህና እውነትን ፖለቲካዊ መሠረት ያደረጉት ናቸው፡፡ እኛ ሁለቱንም ነበረን፤ ዓላማችን የአገራችንን ጥቅምና ክብር ህልውናና ልዕልና ማስከበር ነፃነታችንን ማስጠበቅ ሲሆን፡- ይህም የፍትህና የእውነት ነፍሥ ነው፡፡ በአገር ወዳዱ ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት አማካይነት ደግሞ በአውሮጳ ላይ የወታደራዊ መረጃ ብልጫን ተቀዳጀን፡፡ ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ከውጪ ወራሪዎች ጋር ባደረገቻቸው ጦርነቶች ሁሉ፡- እውነትና ፍትህን መሠረት አድርጋለች፡፡

የዲፕሎማሲያዊ ድሉን የተቀዳጀችው ኢትዮጵያ፡- አውሮጳ ውስጥ ባስቀመጠቻቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወላጅ አባት ራስ መኮንንና ግራዝማች ዮሴፍ በተሰኙ ዲፕሎማቶቿ አማካይነት ነው፡፡ ጣሊያኖች ኢትዮጵያውያን ያልሰለጠኑ በመሆናቸው በምርኮኞች ላይ ሠብአዊነት የጐደለው ድርጊት ይፈፅማሉ ብለው ያስወራሉ፡፡ ግራዝማች ዮሴፍ በተለያዩ ቋንቋዎች እየፃፈ ለአውሮጳ ጋዜጦች ይሄን ያስተባብላሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ልክ ዲፕሎማቶቿ እንዳሉት ምርኮኞችን ግብር አብልታ አካላቸዉም ምቾታቸውም ሳይጓደል ወደ አገራቸው ሰደደች፡፡

በዚህም ዲፕሎማሲያዊ ሥልጣኔዋን ለመላው አውሮጳ እና ለመላው ዓለም በተጨባጭ አሳየች፡፡ ከመቶ ዓመታት በላይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ብቸኛ አፍሪቃዊት አገር፡- ኢትዮጵያ ነች፡፡ የአብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዕድሜ ከስድሣ ዓመት አይዘልም፡፡ ኢትዮጵያ፡- ከኢጣሊያና ከፈረንሣይ ከአሜሪካ (USA) እና ከእንግሊዝ ከሩሢያና ከጀርመን (ከስድስት አገራት) ጋር ከመቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አዳብራ እና አፅንታ ቆይታለች፡፡

የአድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በሠባተኛ ዓመቱ በ1895 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ1903) ከአንድ መቶ ዘጠኝ ዓመታት በፊት አሁን ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ያለበት ሥፍራ ምኒሊክ አደባባይ ነው፡፡ በክብረ በዓሉ (በድል በዓሉ) ላይ ዲፕሎማቶችና የውጪ አገር መንግሥታት ተወካዮች አርበኞች የመንግስት ባለሥልጣኖች ብዙ ሺህ ፈረሰኞችና ሥፍር ቁጥር (ወፈ ሠማይ የሆኑ) ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ መገኘታቸውን፤ ከፈረሰኞቹ ብዛት የተነሳ ፀሐይ በአቧራ እስከመጋረድ መድረሷን ጳውሎስ ኞኞ የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት በተሰኘ መጽሐፉ ላይ ጽፎአል፡፡እንዲሁም ተክለፃዲቅ መኩሪያን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ተመራማሪዎችና የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው ፀሐፍትና ተመራማሪዎች በተለያዩ መፃሕፍቶቻቸው ይሄንን አሣምረው ጽፈውታል፡፡

Related

Lorem ipsum dolor sit amet, consectetur adipiscing elit. Ut elit tellus, luctus nec ullamcorper mattis, pulvinar dapibus leo.
Lorem ipsum dolor sit amet, consectetur adipiscing elit. Ut elit tellus, luctus nec ullamcorper mattis, pulvinar dapibus leo.
error: