ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለፀገች ከመሆኗም በላይ ከወንዞቿ፣ ሀይቆቿ፣ ምንጮቿና ጅረቶቿ ብዛት የተነሳ ‘የአፍሪካ የውሃ ማማ’ በሚል ስያሜ የምትታወቅ ምድር ነች። በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ከሚፈሱ ውሃዎቿ በተጨማሪም አፈሯ ለምና የሰጡትን በብዙ እጥፍ የሚመልስ በመሆኑ ተፈጥሮ ያደላችላት ያስመስላታል።
በርግጥ ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ሀብቶቿ ባሻገር ወደ 120 ሚሊየን የሚገመቱ ዜጎችን በመያዝ በህዝብ ብዛትም የታደለች ሀገር ነች።
ከዚህ አሀዝ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኘው እና አምራች የሆነው ወጣቱ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ የቱን ያህል በተፈጥሮ ሀብቶች ብትታደልና ከ50 በመቶ በላይ ዜጎቿ አምራች ሀይል ቢሆኑም አሁንም ድረስ የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ አልቻለችም።
ሀገሪቱ ምንም እንኳ በተፈጥሮ ሀብቶች የበለፀገች እና ከ50% በላይ ህዝቧ ወጣት ቢሆንም በጦርነት፣ በእርስ በእርስ ግጭት እና በዝናብ እጥረት(በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች) አብዝታ የምትፈተን መሆኗ በምግብ ራሷን ላለመቻሏ በምክንያትነት ይጠቀሳል። ለምሳሌ በመንግስትና ሕወሀት መካከል ላለፉት ሁለት አመታት የተደረገው ጦርነትና በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል ቦረና አካባቢ ለአምስት ተከታታይ አመታት ያጋጠመው የዝናብ እጦት የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ዜጎቿን ቁጥር በ4.6 ሚሊየን ከፍ እንዳረገው የመንግስት መረጃ ያመለክታል።
በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2021 18 ሚሊዬን ዜጎቿ ለምግብ እጦት ተዳርገው የነበረ ሲሆን በቀጣዩ አመት በ2022 ይህ ቁጥር ወደ 22.6 ሚሊዬን ማሻቀቡን ይኸው የመንግስት መረጃ ይጠቁማል። ኢትዮጵያ ካጋጠሟት የውስጥ ችግሮች ማለትም ጦርነትና ተከከታይ የሆነ የዝናብ እጦት ባሻገር እንደ ሌሎቹ የአለም ሀገራት ሁሉ አለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት በእጅጉ ተገዳድሯታል።
ለዚህ ደግሞ በ2019 21.9 % ያህል የነበረው የምግብ እጦት ችግር የተደቀነባቸው ዜጎቿ ቁጥር በቀጣዩ አመት በ3% አድጎ 24.9 % መድረሱን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል። በርግጥ ከዚያ ቀደም በነበሩት ሶስት ተከታታይ አመታት የምግብ እጦት ችግር የተደቀነባቸው ዜጎቿ ቁጥር ማሻቀብ አሳይቷል። የሀገሪቱ መንግስት መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በ2016 14.4% የነበረው በ2017 ወደ 15.7%፤ ይህ አሀዝ በ2018 ወደ 18.2% አድጓል። በዚህም መሰረት በ2016 14.4 በመቶ ዜጎች ብቻ የምግብ እጦት ችግር ተጋርጦባቸው የነበረ ሲሆን ከአራት አመታት በኋላ በ10.5% አድጎ 24.9 % መድረሱን መመልከት ይቻላል።
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ ባለመቻሏ ችግሩ የተከሰተባቸውን ዜጎች ለሰብአዊና ማህበራዊ ቀውስ የሚዳርግ መሆኑ ቢታወቅም በህጻናት ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ ግን እጅጉን የከፋ ነው። ከአምስት አመት በታች ሆነው ሞት ከሚከሰትባቸው ኢትዮጵያዊያን ህጻናት መካከል 45 ከመቶ የሚሆኑቱ ለሞት የሚዳረጉት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው የተነሳ መሆኑን ዩኒሴፍ በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል። ዛሬም ድረስ 39% ወይም 5.4 ሚሊየን ህጻናት (ከ5 ዓመት በታች የሆኑ) የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ለሰውነት መቀንጨር ችግር እንደሚዳረጉም ይኸው መረጃ ይጠቁማል።
መረጃው አያይዞም 21% ህጻናት ሊኖራቸው ከሚገባው ክብደት በታች መሆናቸውን እንዲሁም 58% የሚሆኑ ጨቅላ ህጻናት ስድስት ወር እስኪሆናቸው ድረስ ያለ ምንም ተጨማሪ ምግብ የእናታቸውን ጡት ብቻ ለመጥባት እንደሚገደዱ ይፋ አድርጓል። ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ከአንድ ወር የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አጠቃላይ ህጻናት መካከል 45% የሚሆኑት ብቻ ቢያንስ በቀን ሶስቴ መመገብ የሚችሉ መሆናቸውንም ይኸው የዩኒሴፍ መረጃ ገልጿል።
ይህ አሀዝ የምግብ እጥረቱ ችግር ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በተለየ ሁኔታ እና በከፋ መልኩ በህጻናት ላይ የጭካኔ በትሩን እያሳረፈ እንደሚገኝ የሚያመላክት ነው። ይህንን የህጻናት አስከፊ ችግር ለመቅረፍ በማለም የሀገሪቱ መንግስት በፈረንጆቹ 2015 ‘የሰቆጣ ዴክላሬሽን’ የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ አድርጎ በ2016 ወደ ስራ መግባቱ የሚታወቅ ነው።
ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የበላይ ጠባቂነት የሚመራ ሲሆን ዘጠኝ ሚኒስቴሮች የተካተቱበት እና እስከ 2030 የሚተገበር የ15 ዓመት እቅድ ነው። ምንም እንኳ ይህ ፕሮጀክት መተግበር ከጀመረ ከሰባት አመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም ከሪፖርት በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አለማምጣቱን የሚገልጹ አካላት አሉ። ለዚህ ደግሞ በምግብ እጥረትና ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ ለሞትና እንግልት እየተዳረጉ ያሉትን ህጻናት ቁጥር እየጠቀሱ ፕሮጀክቱ ውጤታማ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ።
በሌላኛው ጫፍ ደግሞ የሰቆጣ ዴክላሬሽን አመርቂና ይበል የሚያሰኝ ውጤት እያመጣ ስለስለመሆኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የፕሮጀክቱ የበላይ ጠባቂ ደመቀ መኮንን ከአስር ወራት በፊት በሰቆጣ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ መግለጻቸው ይጠቀሳል። በእርግጥ በምግብ ራስን የመቻል ችግር የኢትዮጵያ እና የሌሎች ያላደጉ ሀገራት ብቻ እንዳልሆነ የአለም ምግብና እርሻ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ድርጅቱ በ2013 ይፋ እንዳደረገው መረጃ ከሆነ ያደጉት ሀገራች በሀገር ደረጃ በአማካይ 2% የሚሆን ህዝባቸው የምግብ ዋስትናው አልተረጋገጠም። በተመሳሳይ አመት በኢትዮጵያ የምግብ ርዳታ የሚሹትና በዚህ ላይ የሚመረኮዙት ሰዎች ወደ 10% አካባቢ እንደነበር ይኸው መረጃ ጠቁሟል። አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ኃያላን ሀገራትም ጭምር የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ አለመቻላቸውን በዘርፉ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ፊዲንግ አሜሪካ የተሰኘ ፕሮጀክት እንደገለጸው ከ6 ሰዎች አንዱ አሜሪካ ውስጥ ይራባል ወይም የምግብ ዋስትና የለውም:: በአውሮፓዊያኑ 2012 አሜሪካ 49 ሚሊዮን ህዝቧ የምግብ ዋስትና ችግር የተደቀነባቸው ቤተሰቦች እንዳሏት መዘገቡን እዚህ ላይ ማንሳት ይቻላል። ኤም ኤስ ኤን ቢ ሲ ደግሞ የምግብ ዋስትና ችግር ከተደቀነባቸው ውስጥ 1/3ኛ የሚሆኑት ህጻናት ሲሆኑ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የመጨረሻው ደረጃ ሴፍቲ ኔት አካል የሆነው የፉድ ስታምፕ እንኳን አይደርሳቸውም ሲል ይፋ አድርጓል።
ማክሮ ትሬንድስ የተሰኘ ተቋም ይፋ ያደረገው መረጃ ከፈረንጆቹ 2001 እስከ 2020 ባሉት 20 አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ በምግብ እጦት ችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎች ቁጥር መቀነሱን ያሳያል። ይኸው መረጃ እንዳመላከተው በ2001 47% ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠላቸው ሲሆን ከ20 ዓመታት በኋላ በ2020 ይህ ቁጥር ወደ 24.9 አሽቆልቁሏል። በእነዚህ 20 አመታት ውስጥ የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እድገት ማሳየቱን ልብ ይሏል።
በዚህ መረጃ መሰረት በተመሳሳይ የእድገት ደረጃ ላይ ካሉ 23 ሀገራት አንጻር ሲታይም ኢትዮጵያ ከሰንጠረዡ ወገብ ላይ እናገኛታለን። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ከ23ቱ ሰሜን ኮሪያና ሩዋንዳን ጨምሮ ከሌሎች 13 ሀገራት በተሻለ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ስለ ጤና እና ደህንነት ተጨማሪ ጽሁፎችን ለማግኘት በፌስቡክ @TheMosebTimes ላይ ይከተሉን እና ላይክ ያድርጉን።